፭
፩ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤
፪ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና።
፫ ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።
፬ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥
፭ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤
፮ እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ።
፯ የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤
፰ እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤
፱ እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።
፲ የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ።
፲፩ ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው።
፲፪-፲፬ ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።
፲፭ ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።
፲፮ ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤
፲፯-፲፱ መንፈስን አታጥፉ፤
፳-፳፪ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ።
፳፫ የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።
፳፬ የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።
፳፭ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ።
፳፮ ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ።
፳፯ ይህ መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አምላችኋለሁ።
፳፰ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።