፪
፩ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ።
፪ በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር።
፫ አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት።
፬ ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ።
፭ ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።
፮ ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም። ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል?
፯ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ።
፰ ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው። በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ?
፱ ሽባውን። ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?
፲ ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤
፲፩ ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው።
፲፪ ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፥ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና። እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ።
፲፫ ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው።
፲፬ ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው።
፲፭ በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ ይከተሉትም ነበር።
፲፮ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ። ከቀራ ጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ።
፲፯ ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።
፲፰ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም። የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት።
፲፱ ኢየሱስም አላቸው። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም።
፳ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ።
፳፩ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።
፳፪ በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ።
፳፫ በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።
፳፬ ፈሪሳውያንም። እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት።
፳፭ እርሱም። ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥
፳፮ ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው።
፳፯ ደግሞ። ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤
፳፰ እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።