፯
፩ ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።
፪ ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ።
፫ ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥
፬ ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ።
፭ ፈሪሳውያንም ጻፎችም። ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት።
፮ እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች። ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤
፯ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ።
፰ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ።
፱ እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል።
፲ ሙሴ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና።
፲፩ እናንተ ግን ትላላችሁ። ሰው አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥
፲፪ ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤
፲፫ ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።
፲፬ ደግሞም ሕዝቡን ጠርቶ። ሁላችሁ እኔን ስሙ አስተውሉም።
፲፭ ከሰው የሚወጡት ሰውን የሚያረክሱ ናቸው እንጂ ከሰው ውጭ የሚገባውስ ሊያረክሰው የሚችል ምንም የለም።
፲፮ የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ አላቸው።
፲፯ ከሕዝቡ ዘንድ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌውን ጠየቁት።
፲፰ እርሱም። እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን?
፲፱ ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና፤ መብልን ሁሉ እያጠራ አላቸው።
፳ እርሱም አለ። ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው።
፳፩ ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥
፳፪ ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤
፳፫ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል።
፳፬ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ወደ ቤትም ገብቶ ማንም እንዳያውቅበት ወደደ ሊሰወርም አልተቻለውም፤
፳፭ ወዲያው ግን ታናሺቱ ልጅዋ ርኵስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ተደፋች
፳፮ ሴቲቱም ግሪክ፥ ትውልድዋም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፤ ከልጅዋ ጋኔን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው።
፳፯ ኢየሱስ ግን። ልጆቹ በፊት ይጠግቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምናአላት።
፳፰ እርስዋም መልሳ። አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው።
፳፱ እርሱም። ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት።
፴ ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች።
፴፩ ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ አሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ።
፴፪ ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፥
፴፫ እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤
፴፬ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና። ኤፍታህ አለው፥ እርሱም ተከፈት ማለት ነው።
፴፭ ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ።
፴፮ ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት።
፴፯ ያለ መጠንም ተገረሙና። ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ።