፱
፩ በታንኳም ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ።
፪ እነሆም፥ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ አይዞህ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።
፫ እነሆም፥ ከጻፎቹ አንዳንዱ በልባቸው። ይህስ ይሳደባል አሉ።
፬ ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ። ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?
፭ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?
፮ ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፥ በዚያን ጊዜ ሽባውን። ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው።
፯ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ።
፰ ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፥ ለሰውም እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ።
፱ ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው።
፲ በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ።
፲፩ ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን። መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው።
፲፪ ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤
፲፫ ነገር ግን ሄዳችሁ። ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው።
፲፬ በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው። እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት።
፲፭ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።
፲፮ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።
፲፯ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።
፲፰ ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኰንን መጥቶ። ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት።
፲፱ ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው።
፳ እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤
፳፩ በልብዋ። ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና።
፳፪ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና። ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች።
፳፫ ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ።
፳፬ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት።
፳፭ ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች።
፳፮ ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።
፳፯ ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት።
፳፰ ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ ኢየሱስም። ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው። አዎን፥ ጌታ ሆይ አሉት።
፳፱ በዚያን ጊዜ። እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ።
፴ ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ።
፴፩ ኢየሱስም። ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ።
፴፪ እነርሱም ሲወጡ እነሆ፥ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።
፴፫ ጋኔኑንም ካወጣው በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም። እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም እያሉ ተደነቁ።
፴፬ ፈሪሳውያን ግን። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ።
፴፭ ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር።
፴፮ ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።
፴፯ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤
፴፰ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።