፲፫
፩ በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤
፪ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር።
፫ በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው። እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ።
፬ እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፥ ወፎችም መጥተው በሉት።
፭ ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፥
፮ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ።
፯ ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው።
፰ ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።
፱ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
፲ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት።
፲፩ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።
፲፪ ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
፲፫ ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ።
፲፬ መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም።
፲፭ በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል።
፲፮ የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው።
፲፯ እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።
፲፰ እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ።
፲፱ የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው።
፳ በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤
፳፩ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል።
፳፪ በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል።
፳፫ በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።
፳፬ ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች።
፳፭ ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ።
፳፮ ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ።
፳፯ የባለቤቱም ባሮች ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት።
፳፰ እርሱም። ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም። እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት።
፳፱ እርሱ ግን። እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም።
፴ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ።
፴፩ ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤
፴፪ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።
፴፫ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።
፴፬-፴፮ በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው። የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት።
፴፯ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤
፴፰ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤
፴፱ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው።
፵ እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።
፵፩ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥
፵፪ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
፵፫ በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
፵፬ ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፥ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ።
፵፭ ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤
፵፮ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።
፵፯ ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤
፵፰ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፥ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት።
፵፱ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤
፶ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
፶፩ ኢየሱስም። ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን? አላቸው አዎን አሉት።
፶፪ እርሱም። ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል አላቸው።
፶፫ ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ።
፶፬ ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ። ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው?
፶፭ ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን?
፶፮ እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም።
፶፯ ኢየሱስ ግን። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው።
፶፰ በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።