፲፬
፩ በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥
፪ ለሎሌዎቹም። ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።
፫ ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤
፬ ዮሐንስ። እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና።
፭ ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው።
፮ ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤
፯ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት።
፰ እርስዋም በእናትዋ ተመክራ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው።
፱ ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤
፲ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው።
፲፩ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው።
፲፪ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት።
፲፫ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት።
፲፬ ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ።
፲፭ በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት።
፲፮ ኢየሱስም። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው።
፲፯ እነርሱም። ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም አሉት።
፲፰ እርሱም። እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ አላቸው።
፲፱ ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ።
፳ ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ።
፳፩ ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር።
፳፪ ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።
፳፫ ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።
፳፬ ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር።
፳፭ ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።
፳፮ ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ። ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ።
፳፯ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው።
፳፰ ጴጥሮስም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው።
፳፱ እርሱም። ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።
፴ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ።
፴፩ ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና። አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።
፴፪ ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ።
፴፫ በታንኳይቱም የነበሩት። በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት።
፴፬ ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ።
፴፭ የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤
፴፮ የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።